የበጎ ፈቃድ አሻራ በትምህርት ዘርፍ

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያለ ምንም አስገዳጅነት ወይም ቅስቀሳ በራስ ተነሳሽነት የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ በዚህም ሰዎች ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ሀብታቸውን ያለ ምንም ክፍያ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለበጎ ሥራ ያውላሉ፡፡

በክረምት ወራት ከሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት፣ ነፃ ሕክምና፣ የደም ልገሳ፣ የአረንጓዴ አሻራና የተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርት ይገኙበታል፡፡ በተለይም የማጠናከሪያ ትምህርቱ ተማሪዎችን በዕውቀትና በክህሎት በማነፅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

የ‹በልጆቻችን መሃል› የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ወሰን ሰገድ ገብረ ኪዳን እንደገለጹት፣ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን አልፈው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብዙ ተማሪዎችን አለማሳለፋቸው ለወላጆች፣ ለመምህራንና ለማኅበረሰቡ ትልቅ ሥጋትና ፈተና ሆኗል፡፡

በመሆኑም ትውልዱን በዕውቀት ለማነፅና አገርን የሚያቆሙ ባለአዕምሮዎችን ለማፍራት ሲባል በክረምት መርሐ ግብር ነፃ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

አቶ ወሰን ሰገድ እንደተናገሩት፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቱ የሚሰጠው በሁለት መልክ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለአሥረኛ ክፍል ተማሪዎች ከሰኞ እስከ ዓርብ በቋሚነት የሚሰጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የአሥራ አንደኛና የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች በዓርብ ቀን ከታላላቅ ሰዎች የስኬትና የሕይወት ተሞክሮ የሚካፈሉበት ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ዓምና ከእነሱ ጋር ሲማሩ የነበሩት የአሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪዎች በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መመርያ መሠረት በክረምት እንዲማሩ በመደረጋቸው፣ ተማሪዎቹ በሳምንት ለአንድ ቀን ተፈቅዶላቸው መጥተው ከታላላቅ ሰዎች ተሞክሮ እንዲያገኙ ስለሚደረግ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

በዘንድሮው መርሐ ግብር ወደ አሥረኛ ክፍል ለተዛወሩ 40 ተማሪዎች በስድስት የትምህርት ዓይነቶች ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝና በዚህም ሒደት 14 በጎ ፈቃደኛ መምህራን እየተሳተፉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

 

 ‹‹ባለፈው ዓመት የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቱን ስንሰጥ የነበረው ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በሚገኘው ከፍተኛ 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር፤›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ዘንድሮ ግን ተማሪዎቹ የኮሌጅ ሥነ ልቦናና መንፈስ እንዲያዳብሩ በማሰብ ትምህርቱ በየካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡ የዚሁ መርሐ ግብር ተሳታፊዎች ከከፍተኛ 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ 10ኛ ክፍል ከተዛወሩት መካከል በውጤታቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ተማሪዎች ናቸው፡፡

አቶ ወሰን ሰገድ እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓመት የክረምት ማጠናከሪያ የተከታተሉ ተማሪዎች በመደበኛ ትምህርታቸው ውጤታማና የደረጃ ተማሪዎች መሆን ችለዋል፡፡ በተጨማሪም የቀድሞው የምገባ አገልግሎት ዘንድሮ ወደ ገንዘብ ድጋፍ ተቀይሮ ለትራንስፖርትና ለኪስ የሚሆን ከ500 ብር እስከ 1,000 ብር እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡

ትውልድን በዕውቀት ማነፅና በልጆች ትምህርት ላይ መሥራት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፣ አገሪቱን ነገ የሚረከቡት ታዳጊዎች በዕውቀትና በሥነ ምግባር እንዲታነፁ ማድረግ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የክረምት ማጠናከሪያ የሚወስዱ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ዋናው ግብ ሆኖ መያዙን ገልጸዋል፡፡

አቶ ወሰን ሰገድ እንደሚናገሩት፣ ተማሪዎች ከትምህርቱ ባሻገር ስኬታማ ከሆኑ ግለሰቦች ልምድና ተሞክሮ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በዚሁ መሠረት የትምህርት ዘርፍ ባለሙያው ዮሴፍ ውብዓለም (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ ነዋሪና የአካውንቲንግ ባለሙያ የሆኑት አቶ መሸሻ ግርማ፣ አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ ነዋሪና የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፀጋ በሻህ እንዲሁም ፈቃደ አግዋሪ (ዶ/ር) ለተማሪዎቹ ዕውቀት ካካፈሉ፣ የሕይወት ተሞክሯቸውን ካጋሩና ተማሪዎችን ካነቃቁ ግለሰቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የማጠናከሪያ ትምህርቱ በአሜሪካ በሚኖሩት ጥሩነህ ክፍሌ (ዶ/ር) እና በኔዘርላንድስ ነዋሪ በሆኑት አቶ ይገዙ ጋሻው ሐሳብ አመንጪነት እንዲሁም በእርሳቸው አስተባባሪነት የተጀመረ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ መርሐ ግብሩን በዋነኛነት በገንዘብ የሚደግፉት እነዚህ ግለሰቦች ቢሆኑም፣ በተማሪዎቹ ላይ እየተሠራ የሚገኘውን ሥራ በመመልከት ሌሎች ግለሰቦችም ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም መርሐ ግብሩን ይበልጥ በማጠናከር በርካታ አዳዲስ ተማሪዎችን ለውጤት ለማብቃት እየተሠራ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ተማሪዎቹ በ’ንባብ ለሕይወት’ መርሐ ግብር ተሳታፊ በመሆን ከተለያዩ ደራስያን ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ለተማሪዎቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ላመቻቸውና የትምህርት መሣሪያዎችን በሽልማት ላበረከተው የመርሐ ግብሩ አዘጋጅ ለአቶ ቢንያም ከበደ፣ አቶ ወሰን ሰገድ በተማሪዎቹ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርት ላይ አሻራቸውን ላኖሩት ለየካ ኢንዱስትሪ ልማት ኮሌጅ፣ ለወ/ሮ ፍሬዓለም ሺባባውና ለሌሎች አካላት ሁሉ ሥራ አስኪያጁ በድርጅታቸው ‹በልጆቻችን መሃል› ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
https://ethiopianreporter.com/158821/

የ2018 የ"በልጆቻችን" መሀል የክረምት ማጠናከሪያ ትምሕርት ተጀመረ

ይህ የክረምት መርሃ ግብር የተጀመረው ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓም ነው። በዚህ ዓመት መርሃ ግብራችን 40 የአስረኛ ክፍል፣ እንዲሁም 40 የአስራ አንደኛ ክፍል ተጠቃሚዎች ይሆናል። የዘንድሮው የክረምት መርሃ ግብራችን የሚካሄደው በየካ ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ሲሆን፣ ይህም ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ ገብቶ የመማር ስሜት እንዲያድርባቸው ታስቦ የተደረገ ነው።
በዚህ የሁለት ወር ፕሮግራም 14 በጎ ፈቃደኛ መምህራን ይሳተፋሉ። ከ10 በላይ ስኬታማ ዕውቅ ምሁራን ለልጆቻችን የማነቃቂያ ንግግር ያደርጋሉ።
ከውጭ ሀገር ለእረፍት ወደ ሀገር ቤት የመጡ ዳያስፖራ ምሁራን ለልጆቻችን ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ዕቅድ ተይዟል።

የ2017 የክረምት ሥልጠና ፕሮግራም በስኬት ተጠናቀቀ

ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የ8 ሳምንት የበጋ ሥልጠና ፕሮግራማችን በስኬት መጠናቀቁን በኩራት እናስታውቃለን። በግምት 30 ተማሪዎች በአይቲ፣ ሒሳብ፣ ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ እና እንግሊዘኛ ትምህርቶች ላይ ያተኮረ ከፍተኛ ሥልጠና ተሳትፈዋል። ፕሮግራሙ ተደማጭነት ያላቸው የማህበረሰብ አባላት እና ባለሙያዎች የህይወት ተሞክሮአቸውን በማጋራት ተማሪዎች በትምህርታቸው እና ወደፊት ሙያቸው የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አበረታቷል። ሥልጠናው የተማሪዎችን የትምህርት እውቀት ከማጠናከር ባሻገር በራስ መተማመን፣ ሂሳዊ አስተሳሰብ እና የቡድን ሥራ ክህሎት ላይ ከፍተኛ አሻራ ትቷል።